የውሃ ኮዳችን ለበሽታ እንደሚያጋልጠን ልብ ብለዋል? እንዴት ማፅዳት አለብን? ምን ዓይነት ኮዳ እንጠቀም?

የምትጠጣበትን ኮዳ የምታጥብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከኮዳዎ ውሃ በተጎነጩ ቁጥር ወደ ውስጡ ባክቴሪያዎችን እያስገቡ እንደሆነ ያውቃሉ?

እነዚህ ባክቴሪያዎች በቀኑ መጨረሻ ላይ በሚሊዮኖች እንደሚበዙስ? ምናልባት ሰውነትዎን በውሃ ማረስረስዎን እንጂ ስለ ባክቴሪያዎች ትኩረት ሰጥተው ላያውቁ ይችላሉ።

ሆኖም ሥራ ቦታ፣ ስፖርት ቤት አሊያም በየዕለት እንቅስቃሴያችን የምንገለገልባቸው የውሃ ኮዳዎች ለጤና ቀውስ ሊዳርጉን ይችላሉ። ይህንን አስቀድሞ ለመከላከል ምን ማድረግ እንደሚገባ ተመራማሪዎች የሰጡትን ምክር እናካፍላችሁ።

ካርል ቤንኪ በአሜሪካ፣ ኢንዲያና በሚገኘው ፐርዱ የኒቨርሲቲ የምግብ ደኅንነት ባለሙያ ናቸው።

ቤንኪ የውሃ ኮዳቸው ምን ያህል ንጹህ እንደሆነ ያሳስባቸው ነበር። አንድ ቀን የኮዳቸውን የውስጥ ክፍል ሶፍት አስገብተው ሲጠርጉት እጅጉን ነበር የደነገጡት።

"ሶፍቱ ኮዳው ውስጥ ከመግባቱ በፊት ቀለሙ ነጭ ነበር" ይላሉ የሶፍቱ ቀለም ምን ያህል እንደተለወጠ ሲገልጹ።

ቤንኪ እጃቸውን ወደ ኮዳቸው ውስጣዊ ክፍል ሲልኩም ለስላሳ ሆኖ ነበር ያገኙት። ይህ የሆነው በተሠራበት ቁሳቁስ ምክንያት ሳይሆን በባክቴሪያዎች ክምችት መሆኑን እንደተረዱም ይገልጻሉ።

በዚህም ምክንያት ቀጣይ እርምጃቸውን ያደረጉት ጥናት መሥራት ላይ ነበር።

ቤንኪ እና ባልደረቦቻቸው በመሥሪያ ቤታቸው ኮሪደር ላይ የሚተላለፉ ሰዎችን በማስቆም ለጥናታቸው የውሃ ኮዳዎቻቸውን እንዲያውሷቸው በመጠየቅ ነበር ጥናታቸውን ጀመሩት። ይህን ያደረጉት ኮዳዎቻቸው ምን ያህል ንጹህ እንደሆኑ ለማየት ነበር።

ቤንኪ እንደሚሉት ከጥናት ፕሮጀክቱ የተገኘው አስገራሚው ነገር በርካቶቹ የጥናቱን ውጤት ለማወቅ አልጓጉም ነበር።

እነዚህ ሰዎች የጽዳት ልምዳቸው ደካማ መሆኑን አሊያም ጭራሽኑም የማጽዳት ልምድ እንደሌላቸው ያውቃሉ። በኋላ ላይም የጥናቱ ውጤት የውሃ ኮዳዎቻቸው በባክቴሪያ የተሞላ መሆኑን አረጋግጧል።

በአውሮፓውያኑ 2024 በድጋሚ አገልግሎት የሚሰጡ የውሃ ኮዳዎች ገበያ ዋጋ 10 ቢሊየን ዶላር ነበር።

በጣልያናውያን የጤና እንክብካቤ ሠራተኞች ላይ የተሠራ አንድ ጥናትም ግማሽ የሚሆኑት በድጋሚ አገልግሎት የሚሰጡ የውሃ ኮዳዎችን እንደሚጠቀሙ አመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያካተተ ሌላ ጥናትም ከ50 እስከ 81 በመቶ የሚሆኑት እነዚህን የውሃ መጠጫዎች እንደሚጠቀሙ አሳይቷል።

በእርግጥ ሰዎች በእነዚህ ኮዳዎች ውሃ ይዘው በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በቂ ፈሳሽ መውሰዳቸው የራሱ ሆነ የጤና ጠቀሜታ አለው። ሌሎች በሽታዎችን አስቀድመው መከላከል ይችላሉ።

ታዲያ እነዚህን ኮዳዎች አለመጠቀም ነው የሚበጀው? ወይስ የሚያስከትሉትን ችግር ማስወገድ?

በዚህ ላይ ውሳኔዎትን ከማሳለፍዎ በፊት በቅድሚያ ድጋሚ አገልግሎት በሚሰጡ የውሃ ኮዳዎች ውስጥ ባክቴሪያዎች እንዴት ነው የሚከማቹት? ምን ዓይነት ባክቴሪያዎች ናቸው? የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል።

በውሃ ኮዳዎች ውስጥ ያለው ምንድን ነው?

በዩናይትድ ኪንግደም ሌስተር ዩኒቨርሲቲ የክሊኒካል ማይክሮባዮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕራይምሮስ ፍሪስቶን ከቧንቧ የምንቀዳው ውሃ ሙሉ በሙሉ ከባክቴሪያ የፀዳ አይደለም ይላሉ።

በመሆኑም ይህንን ውሃ በኮዳችን ውስጥ ለጥቂት ቀናት ማስቀመጥ ባክቴሪያዎቹ እንዲያደጉ ያደርጋል።

በሰው ላይ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች በ37 ዲግሪ ሴልሽየስ ሙቀት ውስጥ መኖር ይችላሉ የሚሉት ፍሪስቶን፣ ባክቴሪያዎቹ 20 ዲግሪ ሴልሽየስ ባለው የከባቢ ሙቀት ይባዛሉ።

"በኮዳው ውስጥ ያለው ውሃ፣ ይህ የሙቀት መጠን ባለበት ቤት ውስጥ በሚቆይበት ጊዜም ባክቴሪያዎች እየተራቡ ይሄዳሉ" ይላሉ።

ውሃው ንጹህ ቢሆንም እንኳን በምንጠቀምባቸው ኮዳዎች ውስጥ ሲቆይ ከባክቴሪያዎች ማምለጥ አይችልም።

በሲንጋፖር በፈላ የቧንቧ ውሃ [ሙሉ በሙሉ ባክቴሪያዎች በሞቱበት ውሃ] ላይ የተሠራ አንድ ጥናትም በተጠቀምንባቸው ኮዳዎች ውስጥ ባክቴሪያዎች በፍጥነት እንደሚያድጉ አመልክቷል።

አዋቂዎች በሚጠቀሟቸው ኮዳዎች ውስጥ የሚገኝ ውሃ እስከ ቀኑ ረፋድ ድረስ በአንድ ሚሊ ሊትር ውስጥ በአማካይ 75 ሺህ የሚሆኑ ባክቴሪያዎች የተገኙ ሲሆን፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ ቁጥራቸው ከ1 እስከ 2 ሚሊዮን ደርሶ ነበር።

ታዲያ የእነዚህን ባክቴሪያዎች ዕድገት እንዴት ማዘግየት ይቻላል?

የውሃ ኮዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የባክቴሪያዎችን ዕድገት ለመቆጣጠር የሚረዳው አንደኛው መንገድ በተጎነጨን ቁጥር ኮዳዎቻችንን በማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ እንደሆነ ፍሪስቶን ይመክራሉ። ነገር ግን ይህም ሙሉ በሙሉ የባክቴሪያዎቹን ዕድገት አይገታውም።

በውሃ ኮዳ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባክቴሪያዎች ምንጫቸው ከምንቀዳው ውሃ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ግን ውሃውን በሚጎነጨው ሰው ንክኪ አማካይነት የሚመጡ ናቸው።

የውሃ ኮዳዎትን የስፖርት ማዘውተሪያ ቤት አሊያም ሥራ ቦታ ይዘውት ቢሄዱ ወይም ቤት ውስጥ ቢያስቀምጡት የኮዳው ውጫዊ ክፍል በርካታ ባክቴሪያዎችን መሸከሙ አይቀሬ ነው።

በመሆኑም በተጎነጨን ቁጥር ወደ አፋችን ከሚገቡት ባክቴሪያዎች በተጨማሪ በውጫዊ የኮዳው ክፍል ላይ ያሉ ረቂቅ ተህዋስያንም በቀላሉ ወደ ውሃው ውስጥ እንደሚገቡ ፍሪስቶን ያስረዳሉ።

እጃቸውን በመደበኛነት የማይታጠቡ የውሃ ኮዳ ተጠቃሚዎችም ኮዳዎቻቸው እንደ 'ኢኮሊ' ባሉ ባክቴሪያዎች ይበከላሉ።

"ከተፀዳዱ በኋላ እጅዎን በደንብ የመታጠብ ልማድ ከሌለዎት እንደ ኢኮሊ ያሉ ባክቴሪያዎች በእጅዎ አማካኝነት መዳረሻቸው ከንፈሮችዎ ይሆናሉ" ይላሉ ፍሪስቶን።

የውሃ ኮዳዎትን ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚዋዋሱበት ጊዜም እነዚህን ባክቴሪያዎች ወደ ሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ኖሮቫይረስ በሽታ በዚህ መንገድ በቀላሉ ሊተላለፍ ይችላል። ኖሮቫይረስ ተቅማጥ እና ትውከት የሚያስከትል በባክቴሪያ የሚመጣ በሽታ ነው።

ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ የባክቴሪያ ዝርያዎች በሰው አፍ ውስጥ ይገኛሉ የሚሉት ፍሪስቶን፤ በአንዳችን ላይ በሽታ የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች በሌሎች ላይ ተመሳሳይ በሽታ ላያስከትሉ እንደሚችሉ እና አንዳንዴም በሽታው ኖሮባቸው ላይታወቃቸው እንደሚችል ያስረዳሉ። ይህ የሚሆነው ከበሽታ የመከላከል ሥርዓታችን ጥንካሬ እና ድክመት ጋር በተያያዘ ነው።

ሌላኛው የባክቴሪያዎችን ዕድገት የሚያባብሰው በውሃ ኮዳ ውስጥ ከንጹህ ውሃ ውጪ ሌሎች ፈሳሾችን መጨመር ነው። ከውሃ ውጪ ያሉ ፈሳሾች በውስጣቸው ማይክሮ ባክቴሪያ አላቸው። ለምሳሌ ስኳር ያላቸው መጠጦች የባክቴሪያዎችን ዕድገት የሚያፋጥኑ ሲሆን፣ በኮዳ ውስጥ የሚኖርን ባክቴሪያ ቅርጽ ይለውጣሉ።

"ከንጹህ ውሃ ውጪ ያለ መጠጥ ለባክቴሪያ እና ለፈንገስ አመቺ ነው። በተለይ ደግሞ የፕሮቲን ጭማቂዎች" ይላሉ ፍሪስቶን።

"ወተትን በብርጭቆ ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት አስቀምጣችሁ ታውቁ ከሆነ ስትቀዱት በብርጭቆው ላይ ቀጭን ግድግዳ ሰርቶ ታያላችሁ" የሚሉት ፍሪስቶን፣ ባክቴሪያዎች ይህን ግድግዳ እንደሚወዱት ይናገራሉ።

እነዚህ ባክቴሪያዎች የሚጎዱን እንዴት ነው?

ሁላችንም በሰውነታችን፣ በአፈር እና በአየር ውስጥ በሚገኙ ባክቴሪያዎች ተከበናል። ሆኖም አብዛኞቹ ባክቴሪያዎች ከጉዳታቸው ይልቅ ጠቀሜታቸው ያመዝናል።

እንደ ኢኮሊ ባሉ ባክቴሪያዎች የተበከለ ውሃ ተቅማጥ እና ትውከት ሊያስከትል ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ አይሆንም። ኢኮሊ የበርካታ ባክቴሪያዎች ቡድን ሲሆን፣ በአካባቢያችን በተፈጥሮ የሚገኝ ነው።

ተፈጥሯዊ የሆኑ ተህዋስያን በሰው ልጅ አንጀት ውስጥ መገኘታቸውም የተለመደ ነው። እነዚህ ባክቴሪያዎች ጉዳት የሚያስከትሉት ወደ ፓቶጂን ሲለወጡ ነው። ይህ ማለት እነዚህ ባክቴሪያዎች ጎጂ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸውን ረቂቅ ተህዋስያን ሲይዙ ነው። በዚህም እንድንታመም ያደርጋሉ።

አብዛኞቹ ባክቴሪያዎች ለሰው ልጆች ጎጂ አይደሉም የሚሉት ፍሪስቶን፤ ነገር ግን የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎችን ለበሽታ የመጋለጥ ዕድላቸውን ይጨምረዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎችም በአንጀት ውስጥ ዘላቂ የሆነ እክልን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

"አንጀታችን ሁልጊዜም ይለዋወጣል፣ በአንጀታችን ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ የባክቴሪያ ዝርያዎች ይገኛሉ፤ እነዚህ ባክቴሪያዎች በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው ስለሚለዋወጡ ምን ዓይነት ባክቴሪያዎች እንዳሉ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሆኖም በውሃ ኮዳችን ውስጥ ባሉ ባክቴሪያዎች መመረዝ አዎንታዊ ጥቅም የለውም" ብለዋል።

በአንጀታቸው ውስጥ ያሉት ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን በቅርቡ የወሰዱ ሰዎች ለሌሎች በሽታዎች የሚያጋልጡ ለውጦችን ይመለከታሉ።

ተመራማሪዎች ከውሃ ኮዳ ውስጥ ከተወሰደ ናሙና ላይ በሠሩት ጥናት 'ክልብሴላ ግሪሞንቲ' የተባለ የባክቴሪያ ዝርያ ያገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ባክቴሪያዎች የተህዋስያን ክምችት መሥራት የሚችሉ ናቸው።

እነዚህ ባክቴሪያዎች በጨጓራ እና በአንጀት ውስጥ የማይክሮፍሎራ አካል ሆነው የሚገኙ ሲሆን፣ በቅርብ ፀረ ባክቴሪያ በወሰዱ ሰዎች ላይ ከባድ ተቅማጥ ያስከትላሉ።

በውሃ ኮዳ ውስጥ ፈንገስ ካደገም አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ላይ የህመም ምልክቶች እንዲከሰቱ ያደርጋል። ሆኖም የአንድን በሽታ ምንጭ ነጥሎ ማውጣት በጣም ከባድ በመሆኑ በሳይንሳዊ ጽሑፎች ውስጥ ድጋሚ አገልግሎት ላይ በሚውሉ የውሃ ኮዳዎች አማካኝነት የሚመጣ ከባድ የጤና ችግር ምሳሌ የለም። ይህ ማለት ግን በሽታዎች አልተከሰቱም ማለት አይደለም።

የውሃ ኮዳዋን የምታጥብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የውሃ ኮዳችንን ማጽዳት ያለብን እንዴት ነው?

ቤንኪ ማጥለያ ያለው የውሃ ኮዳ ይጠቀሙ ነበር። ኮዳቸው በባክቴሪያዎች መበከሉን የተረዱት የሚጠጡት ውሃ ጥሩ ያልሆነ ጣዕም ካመጣ በኋላ ነበር።

"ኮዳዬን በፈላ ውሃ ቶሎ ቶሎ ማለቅለቅ እንጂ ከዚያ የዘለለ ብዙም የተለየ ነገር አላደርግም ነበር" ይላሉ።

ኮዳቸውን ባጸዱበት ሶፍት ላይ ባዩት ለውጥ ላይ የተመሠረተው ምርምራቸው ግን የውሃ ኮዳቸው ምን ያህል ቆሻሻ እንደነበር አረጋግጧል።

እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸው ያካሄዱት ይህ ጥናት ሌሎችም የውሃ ኮዳቸውን የማፅዳት ልማዳቸውን እንዲመረምሩ አድርጓቸዋል።

ቤንኪ በጥናታቸው ባገኙት ውጤትም በጥናቱ ላይ ከተሳተፉ 90 ተሳታፊዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የውሃ ኮዳቸውን ከሌሎች ጋር የሚጋሩ ሲሆን፣ 15 በመቶ የሚሆኑት የውሃ ኮዳቸውን አፅድተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ሰዎች ኮዳዎቻቸውን ቢያለቀልቁት አሊያም ቢያጥቡት በባክቴሪያዎች የመበከል ዕድሉን ይቀንሳል። ሆኖም ኮዳዎቻችንን በምን ያህል ጊዜ እንደምናጥብ እና የምናጸዳበት መንገድ መሠረታዊው ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህም ሰዎች ኮዳዎቻቸውን በብሩሽ ወይም በእቃ ማጠቢያ ሳሙና ቢያጥቡት በውስጡ ያሉ ባክቴሪያዎችን መቀነስ እንደሚችሉ ቤንኪ ይመክራሉ።

የምግብ ማቀዝቀዣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ውሃ ከተጎነጨን በኋላ ኮዳችንን ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ የባክቴሪያዎችን እድገት ይቀንሳል።

ቤንኪ እና ባልደረቦቻቸው በሠሩት ጥናት ሻይ፣ ቡና ወይም ጁስ የያዙ ኮዳዎች ንጹህ ውሃ ከያዙት ጋር ሲነጻጸር የተበከሉ ሆነው ተገኝተዋል።

በመሆኑም ኮዳዎትን በደንብ ማጠብዎ የሚጎነጩት ውሃ በባክቴሪያ የተበከለ እንዳይሆን ይረዳል። ምንም እንኳን በኮዳው ውስጥ ያለው ውሃ የታከመ ቢሆንም፣ ፍሪስቶን እንደሚሉት ምራቃችን ከተወሰኑ የምግብ ቅንጣጢቶች ጋር ወደ ኮዳው መግባቱ አይቀርም። ይህም ባክቴሪያዎች በደስታ የሚመገቡት አገኙ ማለት ነው።

በዚህም ምክንያት ኮዳዎትን በቀዝቃዛ ውሃ ብቻ ማለቅለቅ በቂ አይደለም። ፍሪስቶን እንደሚሉት ቀዝቃዛው ውሃ በባክቴሪያዎች የተሠራውን ግድግዳ ማፅዳት አይችልም። በኮዳችን የውስጥ ክፍል የተገነባው ቀጭን የባክቴሪያ ግድግዳ ባክቴሪያዎች ተመቻችተው እንዲኖሩ አመቺ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል።

በመሆኑም የውሃ ኮዳችንን ከ60 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ በፈላ ውሃ ማጠብ እንዳለብን ፍሪስቶን ይመክራሉ። ከዚህም በተጨማሪ የእቃ ማጠቢያ ሳሙና በመጨመር ወይም የፈላ ውሃ በማድረግ ከማለቅለቃችን በፊት ለ10 ደቂቃ መተው ይበጃል።

ከዚያም ኮዳው በአየር እንዲደርቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጥቃቅን ተህዋስያን ለመባዛት እርጥብ የሆነ ቦታን ስለሚመርጡ ማድረቁ እጅጉን ጠቃሚ ነው።

ኮዳዎትን ከተጠቀሙ በኋላ በዚህ መንገድ ማጽዳት ያስፈልጋል። የውሃ ኮዳችን ጠረን እስኪኖረው ድረስ ሳንጠብቅ በሳምንት ለበርካታ ጊዜያት ማጽዳት እንደሚያስፈልግ ፍሪስቶን ያሳስባሉ።

"የውሀ ኮዳዎት መሽተት ከጀመረ መጣል ያለበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል ማለት ነው" ይላሉ ፍሪስቶን።

ኮዳዎትን አጽድተው ከጨረሱ በኋላ ከመንካትዎ በፊት እጅዎትን መታጠብዎን መዘንጋትም የለብዎትም።

መጠቀም የሌለብን የውሃ ኮዳ ይኖር ይሆን?

ምንም እንኳን አንዳንድ ጥናቶች ከብረት ከተሠሩት ይልቅ ከፕላስቲክ የተሠሩ የውሃ ኮዳዎች ለባክቴሪያ ክምችት ምቹ መሆናቸውን ቢያሳዩም፣ ዋናው ጉዳይ ግን የምናጸዳበት መንገድ ነው።

በጣም ንጹህ የሆነ ኮዳ ለማጽዳት ቀላል የሆነ እንደሆነ ፍሪስቶን ያስረዳሉ።

ፍሪስቶን ጨምረውም ውጪኛውን ጨምሮ ሁሉም የኮዳውን ክፍል፣ መምጠጫው (ስትሮው) መጽዳቱን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

ሆኖም ከፕላስቲክ ይልቅ የብረት ኮዳ የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምክንያት አለ።

በኳታር ዌል ኮርኔል የሕክምና ትምህርት ቤት የጤና ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አሚት አብርሃም፣ "ፕላስቲኮች ሲሠሩ ለተጣጣፊነታቸው፣ ለዘላቂነታቸው፣ ሙቀትን እንዲቋቋሙ እና ቀላል ክብደት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚጨመርባቸው ኮሚካሎች አሉ" ይላሉ።

አብርሃም እንደሚሉት እነዚህ የሚጨመሩ ኬሚካሎች ከፕላስቲኩ ጋር የተጣበቁ ስለሆነ ወደ ውሃው መግባታቸው አይቀሬ ነው።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚሉት እንደ 'ቢፒኤ' ዓይነት ያሉ ኬሚካሎች የሆርሞን ሥርዓታችንን ያዛባሉ፤ እንዲሁም ለልብ ህመም፣ ለስትሮክ፣ ለስኳር ህመም እና ለሌሎች ሥር ለሰደዱ በሽታዎች ከመጋለጥ ዕድላችን ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ።

አብርሃም እንደሚሉት እነዚህ ኬሚካሎች ወደ ውሃው ውስጥ ከገቡ ምንም እንኳን ኮዳው ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ ወይም ድጋሚ የምንገለገልበት ቢሆንም ከፕላስቲክ የተሠሩ በመሆናቸው ጥቃቅን የፕላስቲክ ቅንጣጢቶች በኮዳው ውስጥ እንዲከማቹ ያደርጋል። በመሆኑም የብርጭቆ አሊያም ከኒኬል የተሠራ ኮዳ መጠቀም የተሻለ ነው።

ሆኖም ምንም ዓይነት የውሃ ኮዳ ብንጠቀም የምንጠጣው ውሃ በጎጂ ባክቴሪያዎች የተበከለ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ንጽህናውን በአግባቡ መጠበቅ ወሳኝ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል።