እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማት እና የጦር አዛዦች ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት የምናውቀው

በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር መርሀ ግብር "ማዕከል" ላይ ያነጣጠረ ነው ያለችውን ጥቃት ፈጽማለች።

በጥቃቱ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆሴን ሳላሚንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ተገድለዋል።

ከተገደሉት መካከል ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች እንደሚገኙበት የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል። ቢቢሲ እነዚህን ዘገባዎች ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

የእስራኤል ጦር ኢራን አርብ ማለዳ ላይ ወደ 100 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) ማስወንጨፏን እና ማክሸፉን አስታውቋል።

በእስራኤልም በግዛቷ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጇል።

አሜሪካ በጥቃቱ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላት ተናግራለች።

የኢራን ዋና የኒውክሌር ማበልፀጊያ ተቋምን ጨምሮ በበርካታ ስፍራዎች ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

ጥቃቶቹ መቼ እና የት ተከሰቱ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ ሌሊት ከ9 ሰዓት ተኩል ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘግቧል።

የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በቴህራን የሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎች በጥቃቱ መመታታቸውን እና ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን ምሥራቅ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግቧል።

በእስራኤል ደግሞ ነዋሪዎች በተመሳሳይ ሰዓት የአደጋ ጊዜ ደወል ከእንቅልፋቸው የቀሰቀሳቸው ሲሆን፣ የአደጋ ጊዜ የስልክ ማንቂያዎችም ደርሷቸዋል።

የእስራኤል ጦር "በኢራን የተለያዩ አካባቢዎች የኒውክሌር ዒላማዎችን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን" ተናግሯል።

የመጀመሪያው ጥቃት ከደረሰ ከሰዓታት በኋላ ከዋና ከተማዋ በስተደቡብ 225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ናታንዝ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ፍንዳታ መከሰቱን የኢራን መንግሥት ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

በኋላ ላይ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ስፍራውን መምታቱን አረጋግጦ፣ ጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብሏል።

የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት፣ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በናታንዝ የኒውክሌር ተቋም ምንም ዓይነት የጨረር መጠን መጨመር አለመኖሩን የኢራን ባለሥልጣናት እንደነገሩት ገልጿል።

የኤጀንሲው ኃላፊ ራፋኤል ግሮስሲ የኒውክሌር ተቋሞች "በፍፁም ጥቃት ሊደርስባቸው አይገባም" ያሉ ሲሆን፣ እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች "በኒውክሌር ደኅንነት እና ጥበቃ እንዲሁም በክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አንድምታ አላቸው" ብለዋል።

ኃላፊው ለቦርድ አባላት በሰጡት መግለጫ "የኒውክሌር ተቋሞችን ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ በኢራን፣ በአካባቢው እና በሌሎችም ሕዝቦች ላይ ከባድ መዘዝን የሚያስከትል አደጋ አለው " ካሉ በኋላ "ሁሉም አካላት ግጭቱ የበለጠ እንዳይባባስ ከፍተኛ ተአቅቦ እንዲያደርጉ" ጥሪ አቅርበዋል።

እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት የሚያሳይ ካርታ

እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት ተደረሰ?

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደተናገሩት ጥቃቱ፣ 'ራይዚንግ ላዮን' ባሉት ዘመቻ "ኢራን የእስራኤል ሕልውና ላይ አደጋ ላይ እንዳትጥል ለማድረግ ያነጣጠረ ወታደራዊ ዘመቻ ነው" ብለዋል።

ዘመቻው "ስጋቱን ለማስወገድ የሚፈጀውን ያህል ቀናት" እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ኔታንያሁ ኢራን ከቅርብ ወራት ወዲህ ራሷን "የጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ" እርምጃዎችን ወስዳለች፤ እናም "አሁን ካልቆመ ኢራን በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት ትችላለች" ብለዋል።

አንድ የእስራኤል ጦር ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢራን "በቀናት ውስጥ" የኒውክሌር ቦንብ ለመሥራት የሚያስችል በቂ የኒውክሌር ክምችት አላት ።

ኔታንያሁ በንግግራቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን "የኢራንን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራም በመጋፈጣቸው" አመስግነዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው አሜሪካ ከኢራን ጋር በኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ በሚያዝያ ወር የጀመረችው ውይይት በቅርብ ቀናት ውስጥ መቀዛቀዝ ባሳየበት ወቅት ነው።

ውይይቱን ለመቀጠል ለእሁድ ቀጠሮ ተይዞ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረቷን እንድታቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋ አድርገው ነበር።

ለረዥም ዓመታት ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ሰላማዊ እንደሆነ አጥብቃ ትናገራለች።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ ከኔታኒያሁ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት የኢራንን የኒውክሌር አቅምን በተመለከተ ከወታደራዊ እርምጃ ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ መንገድን ስለመከተል "የከረረ" ንግግር ማድረጋቸው ተዘግቧል።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ እና ጥቅምት ወር ላይ ኢራን እና እስራኤል፣ ምንም እንኳን እስራኤል ባለፈው ዓመት የፈጸመችው ጥቃት አሁን ከምታደርገው አንፃር ሰፊ ነው ባይባልም፣ በርካታ የአየር ጥቃቶችን አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ፈጽመዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

"ጥቃቱ ጦርነት ማወጅ ነው"

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኔይ እስራኤል "ከባድ ቅጣት እንደሚደርስባት መገመት አለባት" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ደግሞ ጥቃቱን "የጦርነት አዋጅ" ሲሉ ገልጸውታል።

ኢራን አርብ ጧት ወደ 100 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን እና ማምከኑን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገሪቱ ጦር "የኢራንን ሉዓላዊነት በሙሉ ኃይል እና ተገቢ ነው ብሎ ባሰበው መንገድ ከመከላከል ወደ ኋላ አይልም" ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ የእስራኤልን ዘመቻ "የትንኮሳ ድርጊቶች" ሲል የገለፀ ሲሆን፣ "የአሜሪካ መንግሥት የዚህ አገዛዝ ዋነኛ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ኃላፊነቱንም ይወስዳል" ብሏል።

ካርታ

"ኢራን ሳይረፍድ ስምምነት ላይ መድረስ አለባት"

ዶናልድ ትራምፕ ለጥቃቱ በሰጡት ምላሽ ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ "ተደጋጋሚ ዕድል" የተሰጣት ቢሆንም "እነርሱ ግን ሊስማሙ አልቻሉም" ብለዋል።

አንዳንድ የኢራን ባለሥልጣናት "በድፍረት ተናግረዋል፤ ነገር ግን ምን ሊፈጠር እንደሆነ አላወቁም ነበር" ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ጽፈው "አሁን ሁሉም ሞተዋል" ብለዋል።

"ቀድሞውንም ሞት እና ውድመት ደርሷል፣ ነገር ግን ይህን እልቂት ለማስቆም አሁንም ጊዜ አለ፣ ቀጣዮቹ የታቀዱት ጥቃቶች የበለጠ የከፉ ናቸው፤ ወደ ስምምነት ኑ።

"ኢራን ሁሉ ነገር ባዶ ከመሆኑ በፊት ስምምነት ማድረግ እና በአንድ ወቅት የኢራን ኢምፓየር ተብሎ ይጠራ የነበረውን ማዳን አለባት። ከዚያ ሞትም ሆነ ጥፋት የለም። ከመርፈዱ በፊት አሁኑኑ አድርጉት! በቃ!"

ቀደም ሲል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዩናይትድ ስቴትስ በጥቃቱ ምንም ዓይነት ድጋፍ ለእስራኤል አለማድረጓን እና ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳልሰጠች ተናግረው ነበር።

የአሜሪካ ዋነኛ ትኩረት በአካባቢው የሚገኙትን የአሜሪካ ኃይሎችን መጠበቅ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ እና የኢራን የኒውክሌር ድርድርን በማሸማገል ላይ ያለቸው ኦማን እስራኤል ለተፈጠረው "መካረር እና መዘዙ" ተጠያቂ ናት ብላለች።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር ስለጥቃቶቹ የተሰማው "አሳሳቢ ነው" ካሉ በኋላ የፈረንሣይ መንግሥት እንዳለው ውጥረት እንዲረግብ አሳስበዋል።

የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔኒ ዎንግ ጥቃቱ "ቀድሞውንም ወዳልተረጋጋው አካባቢ የበለጠ አለመረጋጋት ሊያመጣ ይችላል" ብለዋል።

ጥቃቱን ጃፓን፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዢያ እና በሳዑዲ አረቢያም አውግዘውታል።

ቻይና ጥቃቶቹ ሊያመጡ የሚችሉት አስከፊ መዘዞች በጣም እንዳሳሰባት ተናግራለች።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ "በምንም ዓይነት ሁኔታ ወደ ዘላቂ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ" ሁለቱም ወገኖች "ራሳቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያቅቡ" ጠይቀዋል።

የኢራን እስላማዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆሴን ሳላሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጥቃቱ የተገደለው ማን ነው ?

የእስራኤል መከላከያ ሦስት የኢራን ወታደራዊ አዛዦች "እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ተወግደዋል" ብሏል።

እነሱም ሆሴን ሳላሚ፣ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ፣ ጎላማሊ ራሺድ የካታም አል አንቢያ ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ እና የኢራን ጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ መሐመድ ባገሪ ናቸው።

የኢራን መንግሥት በበኩሉ የአየር ኃይሉ አዛዥ አሚር አሊ ሃጂዛዴህ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር መገደላቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል ጦር የሌሊት ጥቃቱ ያተኮረው "የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እና የኒውክሌር መርሃ ግብር መሪዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ነው" ብሏል።

ከኢራን ጦር ጋር ግንኙነት ያለው የዜና ወኪል ታስኒም እንደዘገበው በጥቃቱ ስድስት የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መሞታቸውን አስታውቆ፣ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ስማቸው ተዘርዝሯል።

  • ፌሬይዶን አባሲ የቀድሞ የኢራን አቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት መሪ
  • መሐመድ ማህዲ ቴህራንቺ - በኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራም ውስጥ የተሳተፉ
  • አብዱልሃሚድ ሚኑችህር - በሻሂድ ብሄሽቲ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ኢንጂነሪንግ ኃላፊ
  • አህመድ ረዛ ዞልፋጋሪ - በሻሂድ ብሄሽቲ ዩኒቨርሲቲ የኑክሌር ምህንድስና ፕሮፌሰር
  • አሚርሆሴን ፈቂ - በሻሂድ ብሄሽቲ ዩኒቨርሲቲ የኑክሌር ፕሮፌሰር

የአያቶላህ አሊ ካሜኒ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አሊ ሻምካኒም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከተገደሉት መካከል ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ይገኙበታል።

ቢቢሲ እነዚህን ዘገባዎች ከገለልተኝነት ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምንድን ነው?

ለረዥም ዓመታት ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሲቪል ዓላማ ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል ስትናገር ቆይታለች።

በኢራን የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በርካታ የኒውክሌር ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፣ ቢያንስ የተወሰኑት በእስራኤል ጥቃቶች ዒላማ ተደርገዋል።

ነገር ግን ብዙ አገራት እንዲሁም ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ የኢራን ፕሮግራም ለሲቪል ዓላማ ብቻ ይውላል የሚለው መከራከርያ አላሳመናቸውም።

በዚህ ሳምንት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ኢራንን ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ማስፋፊያ ላለማድረግ የገባችውን ግዴታ መጣሷን በይፋ ተናግሯል።

ስለ ማይታወቁ የኒውክሌር ቁሳቁሶች እና የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ሙሉ መልስ ለመስጠት የኢራን መንግሥት "ዳተኛ" መሆኑን ጠቅሷል።

ኤጀንሲው ቀደም ሲል ያወጣው ሪፖርት ላይ ኢራን ዩራኒየምን ወደ 60 በመቶ አበልጽጋለች። ይህም ዘጠኝ የኒውክሌር ቦምቦችን ለመሥራት በቂ ነው።