ተቃዋሚዎች ትራምፕ ካሰማሯቸው ወታደሮች ጋር የተፋጠጡባት ሎስ አንጀለስ

የብሔራዊ ጥበቃ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃን ተከትሎ በሎስ አንጀለስ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቀናትን አስቆጥሯል።

ተቃውሞው ተቀጣጥሎም ትራምፕ የአገሪቱ የብሔራዊ ጥበቃ አባላት የሆኑ ወታደሮችን አሰማርተዋል።

ሰልፈኞች የከተማዋን ማዕከላዊ ክፍል የሚያቋርጠውን ዋነኛ መንገድ የዘጉ ሲሆን፤ ይህም የተሽከርካሪዎችን ፍሰት ዘግቷል።

ሁዋን እና በርካታ ጓደኞቹ በሎስ አንጀለስ በሚገኝ አንድ የመለዋወጫ እቃዎች መደብር በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ተሰባስበዋል።

በዚህ ስፍራ ነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር የያዙትን ፖሊሲ በመቃወም የተቀጣጠለው የሎስ አንጀለሱ ፍጥጫ መነሻው።

በተለምዶ በዚህ ስፍራ የቀን ሰራተኞች ይሰባሰባሉ።

አብዛኞቹ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ሲሆኑ በዚህች ስፍራም ከተገበያዮች ወይም ከቀጣሪዎች ስራ የሚፈልጉበት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

መደብሯ የስደተኞች የተቃውሞ ማዕከል ከሆነች ከአንድ ቀን በኋላ ግን ቁጥራቸው ቀንሷል።

እሁድ እለት ከ82 በመቶ ሂስፓኒክ ተብለው የሚጠሩ የስፓኒሽ ቋንቋ ነዋሪዎች በአብዛኛው መኖሪያ በሆነችው ፓራማውንት በተባለችው ሰፈር በምትገኘው መደብር ጥቂት ሰራተኞች ናቸው የነበሩት።

በጣሪያ ስራ በጥገና ወይም በቀለም ስራዎች እናግዛለን የሚል ማስተዋወቂያ የለጠፉ ሁለት ትናንሽ መኪኖች አጠገብ ቆመዋል።

ተቃውሞው መነሻው የሆነው የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት የቀን ሰራተኞችን በድንገተኛ ሁኔታ ከበው አስረዋቸዋል የሚሉ ዜናዎች ናቸው።

የአካባቢው ነዋሪዎች የኢሚግሬሸን ባለስልጣናት መኪኖችን በስፍራው ማየታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሎስ አንጀለስ በአሜሪካ ካሉ ከተሞች አናሳ የሚባሉ ሂስፓኒክ ማህበረሰቦች በአብዛኛው የሚኖሩባት ናት።

ሁኔታው ከፍተኛ ፍርሃትና ድንጋጤን ፈጠረ።

ከዚያም ሆም ዲፖ በሚባለው ትልቁ የቤት ዕቃዎች መሸጫ እና በአሜሪካ በርካታ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ስራ ለማግኘት በሚሄዱበት ቦታ ላይ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ወረራ እና የቀን ሰራተኞችን እያሰሩ ነው የሚል ሪፖርት ተከተለ።

በዚህች የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚበዙባት ከተማ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ወደ ሁከት ተቀየረ። ድንጋይ እና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ተወረወሩ።

ባለስልጣናቱ በበኩላቸው አስለቃሽ ጭስ፣ የፕላስቲክ ጥይት፣ የሚያቃጥል ፈሳሽ (ፔፐር ስፕሬይ) በተቃዋሚዎች ላይ ተጠቅመዋል።

ነገር ግን በፓራማውንት በሆም ዲፖ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከተሳሳተ መረጃ የተነሳ እንደሆነ ባለስልጣናቱ ይናገራሉ።

ምንም እንኳን በርካታ ስደተኞች በሌሎች ስፍራዎች በኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ተይዘዋል።

በመደብሩ ወረራ ተፈጽሞ የቀን ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል የሚለው የተሳሳተ መረጃ እንደነበር የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ አስታውቋል።

"ሎስ አንጀለስ ባለው ሆም ዲፖ መደብር በአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለስልጣን (አይስ) የተፈጸመ ወረራ የለም፤ ሃሰተኛ ሪፖርት ነው" ሲል ቢሮው ገልጿል።

ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ከቶዮታ ፒክአፕ መኪና አጠገብ የነበረው ሁዋን " ስለሆነው ጉዳይ ማንም አያውቅም። ሁሉም ፍራቻ ላይ ነው" ይላል።

መኪኖች የተቃጠሉበት እና የንግድ ተቋማት የተዘረፉበት በፓራማውንት የተፈጠረው አለመረጋጋት የፌደራል ባለስልጣናት በሎስ አንጀለስ አካባቢ ለተፈጠረው ሁከት መነሻ ሆኗል ይላሉ።

ቅዳሜ ዕለት፣ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው ተቃውሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የአገሪቱ ብሔራዊ ጥበቃ እንዲሰማራ አድርገዋል።

በተለምዶ የግዛቲቷ ገዥ ናቸው የአገሪቱ ብሔራዊ ጥበቃ ስምሪትን በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጡት።

በማግሥቱ እሁድ ተቃውሞው ሶስተኛ ቀኑን ሲይዝ የታጠቁ የብሔራዊ ጥበቃ ወታደሮች ከመለዋወጫ ዕቃዎች መደብር መንገድ ተሻግሮ ባለ አንድ የንግድ ፓርክን አጥረው ቆመው ታይተዋል።

ወታደራዊ መኪኖች በቆሙበት ስፍራ ተቃዋሚዎች ኃይለ ቃል እየሰነዘሩ እና የሜክሲኮ ሰንደቅ ዓላማ እና ባነሮችን እያውለበለቡ ታይተዋል።

የአሜሪካ የአገር ውስጥ የደህንነት ቢሮ እንደገለጸው በዚህ ሳምንት በሎስ አንጀለስ አካባቢ 118 ህገወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አምስት የወሮበላ አባላት ቡድን መሆናቸው ተገልጿል።

ሆም ዲፖ የተነሳው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከእነዚህ ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ ጥቃት እና ዝርፊያን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የወንጀል ታሪክ አላቸው ብሏል።

ትራምፕ በበኩላቸው በሎስ አንጀለስ ተቃውሞ የወጡትን "አማጺያን ናቸው"፤ "ከዚህ የሚያመልጡበት መንገድ የለም" ብለዋል።

በከተማዋ የተፈጠረው ግርግር በዚህ መልኩ መቀየሩ እንደ ዶራ ሳንቼዝ ላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች አስደንጋጭ ሆኗል።

ከተቃውሞው ማዕከል አቅራቢያ በሚገኝ አንዲት ቤተ ክርስቲያንም ዕሁድ እለት ከማህበረሰቡ አባላት ጋር ተሰባስበው ነበር።

በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በስፍራው የሚኖሩ የሂስፓኒክ ማህበረሰብ ምን ያህል ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው እየተወያዩ ነበር።

ወታደሮች የተሰማሩበት ይህ ግርግር ለስደተኛው ማህበረሰብ ምን ያህል መሸርሸር ሊያመጣ እንደሚችልም ነው ዶራ የምትናገረው።

ሎስ አንጀለስ በአሜሪካ ውስጥ ካሉ አናሳ ማህበረሰብ በአብዛኛው ከሚኖሩባት ከተሞች አንዷ ናት።

ሂስፓኒክስ የሚል መጠሪያ ያላቸው ስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች በከተማዋ ከየትኛውም ብሔር የበለጠ ቁጥር አላቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ስደተኞች በተለይም ከደቡብ ሜክሲኮ የመጡት የከተማዋ ባህል እና ታሪክ ዋና አካል ናቸው።

ከተማዋ ከፌደራል የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ጋር እንደማትተባበር እና ለሁሉም ከለላ የምትሰጥ እሰጣለሁ ስትል ትመካለች።

አንዳንዶች የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንት አስተዳደር በሎስ አንጀለስ ህጋዊ ሰነድ በሌላቸው ስደተኞች ላይ ማነጣጠራቸው የነበረው ውጥረት እንዲፈነዳ ማድረጉን ይገልጻሉ።

"መነሳት ነበረብን፤ ጊዜው አሁን ነው" ስትል በፓራማውንት ለተቃውሞ የወጣው ማሪያ ጉቴሬዝ ታስረዳለች።

አክላም "ይህ ህዝቤ ነው" ስትል አክላለች።

ሜክሲኮ የተወለደችው ማሪያ ከህጻንነቷ ጀምሮ አሜሪካ ኖራለች።

እሷ እንደ ሌሎች በርካቶች በህገወጥ መንገድ አሜሪካ ውስጥ እየኖሩ ያሉ የቤተሰብ አባላት እንዳላቸው ይናገራሉ።

"ይህ ሎስ አንጀለስ ነው፤ ሁላችንንም ይነካል"

"ሁሉም ቢሆን ቤተሰብ አለው፤ ወይም ደግሞ ሰነዶች የሌላቸውን ሰዎች ያውቃሉ"

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ተቃዋሚዎች የዳውንታውን አካባቢን በአፋጣኝ ለቅቀው እንዲወጡ አሳስቧል። ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎች እና ጎብኚዎች "ማንኛውንም የወንጀል እንቅስቃሴ እንዲጠነቀቁ እና ሪፖርት እንዲያደርጉ" አሳስቧል።

"የፖሊስ አባላት በተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሰቡ ሰዎች ለመበተን እየተንቀሳቀሱ " መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

የከተማዋ ፖሊስ በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ማስጠንቀቂያ "ዳውንታውን ሎስ አንጀለስ ህገወጥ ስብስብ ተብሎ ታውጇል። በአስቸኳይ የዳውንታውን አካባቢን ለቅቃችሁ እንድትወጡ" ብሏል።