የኤርትራ፣ የሱዳን እና የሶማሊያ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የታገዱባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያን ጨምሮ የአስራ ሁለት ዜጎች በስደተኝነትም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ የሚያግድ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ከመጪው ሰኞ ሰኔ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ለሚሆነው ለዚህ ዕገዳ የተለያዩ ምክንያቶች ከዋይት ሐውስ ተሰጥቷል።

ከእነዚህም መካከል አገራቱ ያላቸው የጉዞ እና የዜግነት ሰነዶች አያያዝ አስተማማኝነት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ከዚህ በፊት ወደ አሜሪካ ገብተው በዚያው የቀሩ ዜጎቻቸው መጠን ተጠቃሽ ናቸው።

ዕገዳው ከተጠላባቸው አገራት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከአፍሪካ ሲሆኑ እነሱም ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ብራዛቪል) ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሊቢያ ሲሆኑ፣ ይህም ማለት ከአስራ ሁለቱ አገራት ሰባቱ ከአፍሪካ ናቸው።

ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ከአፍሪካ ቀንድ እና የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ናቸው። አሜሪካ በኤርትራ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ ዜጎች ላይ ዕቀባውን ስትጥል ምን ምክንያት ሰጠች?

ኤርትራ

በዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ በኤርትራ ዜጎች ላይ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ዕገዳው እንዲጣል ምክንያት የሆኑ ሰበቦችን አስቀምጧል።

በዚህም በኤርትራ ፓስፖርት፣ የዜግነት እና ነዋሪነት መታወቂያ በሚሰጠው ማዕከላዊ ባለሥልጣን ብቃት ላይ አሜሪካ ጥያቄ እንዳላት ተጠቅሷል፤ እንዲሁም የኤርትራ ዜጎች የወንጀል መዛግብት ለአሜሪካ ክፍት አለመሆናቸው ሌላኛው ምክንያት ነው።

በተጨማሪም ኤርትራ ከአሜሪካ የሚባረሩ ዜጎቿን ለመቀበል ፈቃደኛ ያለመሆን ታሪክ ያላት መሆኗ፣ ለዚህም በተለያዩ ቪዛዎች ወደ አሜሪካ የገቡ ኤርትራውያን ከተፈቀደላቸው ጊዜ የመቆየታቸውን ሁኔታ በመቶኛ አስቀምጧል።

በዚህም የኤርትራ ዜጎች በስደተኝነትም ሆነ ከዚያ ውጪ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ሙሉ ለሙሉ ታግደዋል።

ሶማሊያ

በሽብር ቡድንነት በተፈረጀው አል ሻባብ እየተፈተነች ያለችው ሶማሊያም የመንግሥቷ ደካማ መሆን እና በግዛቷ ያለው የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ለአሜሪካ ስጋት መሆኑ ተጠቅሷል።

ዋይት ሐውስ ሶማሊያ ፓስፖርት እና ሌሎች የዜግነት መታወቂያዎችን የሚሰጥ ብቃት ያለው እና ማጣራት እና ምርመራ የሚያደርግ ተባባሪ የሆነ ማዕከላዊ ባለሥልጣን የላትም ሲል በምክንያትነት አስቀምጧል።

እንዲሁም የአገሪቱ መንግሥት "ግዛቱን የመቆጣጠር እና የማስተዳደር ብቃት የለውም ያለ ሲሆን፣ ይህም የሶማሊያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ ያለው ቁጥጥር እና የበላይነትን ውስን ያደርገዋል" ብሏል።

የአሜሪካ መንግሥት "ሶማሊያ የሽብርተኞች መሸሸጊያ ናት" በማለትም ሽብርተኞች ጥቃቶችን ለማቀድ፣ ለማደራጀት እና ለሚፈጸም የአገሪቱን ግዛቶችን እንደሚጠቀሙ አመልክቷል።

በተጨማሪም ሶማሊያ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሆኑ የሽብር ቡድኖችን ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎች መዳረሻ ነች ያለ ሲሆን፣ የሽብር ቡድኖች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ የአገሪቱ መንግሥት ቁጥጥር የማድረግ ፈተና እንደገጠመው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ሶማሊያ ከአሜሪካ የሚባረሩ ዜጎቿን ያለመቀበል ታሪክ ያላት መሆኑን በማመልከት ዜጎቿ በስደተኝነትም ሆነ ከዚያ ውጪ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ሙሉ ለሙሉ መታገዳቸው ተገልጿል።

ሱዳን

ከሁለት ዓመት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን በአሜሪካ የጉዞ ክልከላ ውስጥ የገባችው በመንግሥቷ መዳከም ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።

ዋይት ሐውስ የሱዳን መንግሥት ፓስፖርት እና ሌሎች የዜግነት መታወቂያዎችን የሚሰጥ ብቃት ያለው፣ ማጣራት እና ምርመራ የሚያደርግ ተባባሪ የሆነ ማዕከላዊ ባለሥልጣን የላትም ብሏል።

በተጨማሪም በተለያዩ ቪዛዎች ወደ አሜሪካ የገቡ ሱዳናውያን ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የመቆየታቸውን ሁኔታ በመቶኛ ተጠቅሶ አሁን ለተጣለው ክልከላ ምክንያት ተሰጥቷል።

በዚህም የሱዳን ዜጎች በስደተኝነትም ሆነ ከዚያ ውጪ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ሙሉ ለሙሉ ታግደዋል።

ዶናልድ ትራምፕ አሁን ባወጡት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን በተጨማሪ አፍጋኒስታን፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ብራዛቪል)፣ ሄይቲ፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ምንያማር እና የመን ይገኙበታል።

በተጨማሪም የብሩንዲ፣ የኩባ፣ የላኦስ፣ የሴራሊዮን፣ የቶጎ፣ የቱርክሜኒስታን እና የቬንዙዌላ ዜጎች ደግሞ ከፊል የዕገዳ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።