የዩክሬን ድሮኖች በሩሲያ የጦር ጄቶች ላይ ከባድ የተባለ ጥቃት ፈፀሙ

በአንደኛው ጥቃት በየተፈጠረ ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በአንደኛው ጥቃት በየተፈጠረ ጭስ

ዩክሬን በአራት የሩሲያ ወታደራዊ ካምፖች የሚገኙ 40 የጦር አውሮፕላኖች ላይ ተከታታይ ከባድ ጥቃቶችን መፈጸሟን አስታወቀች።

ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በጥቃቱ 117 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልፀው "34 በመቶ [የሩሲያ] ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳዔል ተሸካሚዎችን" መምታታቸውን ተናግረዋል።

የዩክሬን ደኅንነት ተቋም ጥቃቱን ለመፈጸም ለአንድ ዓመት ከግማሽ ያህል ሲያቅድ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ሩሲያ በአምስት ግዛቶቿ ላይ "የሽብር ተግባር" መፈፀሟን አስታውቃለች።

ጥቃቱ የተፈጸመው የሩሲያ እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች ዛሬ ሰኞ ለሁለተኛ ዙር ድርድር ቱርክ ኢስታንቡል ከመገናኘታቸው በፊት ነው።

ሁለቱ አገራት ጦርቱን ለማጠናቀቅ ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ተከትሎ በሁለተኛ ዙር ድርድር ውጤት ይመጣል ተብሎ እንደማይገመት ታዛቢዎች ተናግረዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከባድ የሆነ የሚሳዔል ጥቃት እና የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።

የሩሲያ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ፣ ሪያ በበኩሉ የአገሪቱ የደኅንነት መሥርያ ቤት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ታቅዶ የነበረን ጥቃት ማክሸፉን ዘግቧል።

ሁለት ግለሰቦች በፕሪሞሪ ግዛት በባቡር ሀዲድ ላይ አሻጥር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘግቧል።

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ወረራ ከፍተው እስካሁን ጦርነት እየተካሄደ ነው።

ሞስኮ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓውያኑ 2014 ከዩክሬን በኃይል የያዘቻት ክሬሚያን ጨምሮ የአገሪቱን 20 በመቶ ግዛት ትቆጣጠራለች።

የዩክሬን የደኅንነት ተቋም ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ እንደተናገረው በሩሲያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ወደ አየር ኃይል የጦር ሰፈር አቅራቢያ በስውር በተጠጉ ከርቀት ቁጥጥር በሚደረግባቸው እና "በትክክለኛው ሰዓት" ዒላማቸውን እንዲመቱ በተደረጉ ድሮኖች መሆኑን ተናግሯል።

እሁድ ረፋዱ ላይ በበርካታ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ዜሌንስኪ የደኅንነት ተቋማቸው ኃላፊን ቫሲል ማሊኡክን አሞግሰው "ድንቅ የሆነ ውጤት" ሲሉ የተካሄደውን ጥቃት አድንቀዋል።

ጥቃት ያደረሱት 117 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እያንዳንዳቸው የራሳቸው አብራሪ እንደነበራቸው ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

የድሮን ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, SBU source

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የዩክሬን ፕሬዝደንት አክለውም "በጣም የሚያስደንቀው ነገር፤ እና ይህንን በይፋ መናገር እንችላለን፣ በሩሲያ ግዛት ውስጥ የእኛ ኦፕሬሽን 'ቢሮ' ከክልሎቻቸው በአንዱ ከሩሲያ የደኅንነት ቢሮ አጠገብ ይገኛል።"

ዜሌንስኪ በጥቃቱ ላይ የተሳተፉ በሙሉ ሩሲያ ምላሽ ከመስጠቷ በፊት በሰላም ወደ ዩክሬን መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የዩክሬን የደኅንነት ተቋም በሩሲያ ወሳኝ የአየር ኃይል ምድብ ላይ የደረሰውን ውድመት 7 ቢሊዮን ዶላር የገመተ ሲሆን፣ ተጨማሪ መረጃ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

ዩክሬን አደረስኩ ያለችው የጉዳት መጠን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት አራት የሩሲያ የአየር ኃይል ጦር ሰፈሮች፣ ሁለቱ በሺህዎች ኪሎ ሜትሮች ከዩክሬን የራቁ ናቸው፣ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረው ነበር።

ምንጮቹ አክለውም ጥቃት ከደረሰባቸው የሩሲያ ጦር ጄቶች መካከል ስትራቴጂክ ኒውክሌር ቦምብ መሸከም የሚችሉት ቲዩ-95 እና ቲዩ-22ኤም3 እንዲሁም ለቅድመ ማስጠንቀቅያ የሚያገለግለው ኤ-50 የተሰኘው አውሮፕላን ይገኝበታል።

እንደ ዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት መረጃ ምንጮች ከሆነ መጀመሪያ ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ በድብቅ ወደ ሩሲያ ገብተዋል።

ከዚያም በእንጨት ሳጥን ውስጥ ተደርገው በጭነት መኪኖች ወደ አየር ኃይል ሰፈሮቹ እንዲጠጉ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

"በትክክለኛው ጊዜ፣ ጣሪያዎቹ በርቀት ተፍተው ድሮኖቹ የሩሲያ ጄቶችን መደብደብ ጀመሩ።"

የኢርኩትስክ ግዛት አስተዳዳሪ ኢጎር ኮብዜቭ በሰሬድኒ፣ ሳይቤሪያ የሚገኘውን የቤላያ ጦር ሰፈርን ያጠቁ ድሮኖች ከጭነት መኪና መነሳታቸውን አረጋግጠዋል።

ሌሎች ጥቃቶችም በተመሳሳይ ከጭነት መኪኖችቹ በተነሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መፈፀማቸውን የሩሲያ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሠራጨው ጽሑፍ በአገሪቱ አምስት ክልሎች በሚገኙ የአየር ማረፊያዎች ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጧል።

በኢቫኖቮ፣ ራያዛን እና አሙር ክልሎች በሚገኙ ወታደራዊ አየር ማረፊያዎች ላይ ጥቃት የደረሰ ቢሆነብም "ሁሉም ጥቃቶች ተቀልብሰዋል" ሲል ተናግሯል።

የሩሲያ መከላከያ በሙርማንስክ እና ኢርኩትስክ ክልሎች ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአቅራቢያው ያሉ የአየር ኃይል ጦር ሰፈሮችን ካጠቁ በኋላ "በርካታ አውሮፕላኖች ተቃጥለዋል" ብሏል ።

ሁሉም ቃጠሎዎች መጥፋታቸውን እና በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ገልጿል። "በሽብር ጥቃቱ ከተሳተፉት መካከል የተወሰኑት በቁጥጥር ስር ውለዋል" ሲልም አክሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ባለሥልጣናት ትናንት ምሽት በዩክሬን ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 472 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሰባት ባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳዔሎች ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።

ዩክሬን 385 የአየር ላይ ዒላማዎችን "አምክኛለሁ" ብላለች።