ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከባድ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ትራምፕ ፑቲንን "እብድ" ሲሉ ዘለፉ

ትራምፕ እና ፑቲን

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲንን "እብድ" ሲሉ ዘለፉ።

ትራምፕ "ደስተኛ እንዳልሆኑ" እና ጠንከር ባለ እና ባልተለመደ ተግሳጽ ፑቲንን "ምን ነካው? ብዙ ሰዎችን እየገደለ ነው" ብለዋል።

በኋላም ፑቲንን "ፍጹም እብድ" በማለት ወርፈዋቸዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች ላይ የአሜሪካ ዝምታ ፑቲንን እያበረታታ ነው ሲሉ ቀደም ብለው ተናግረው ነበር።

በሩሲያ ላይ ከበድ ያሉ ማዕቀቦችን ጨምሮ "ጠንካራ ጫና" እንዲደረግባት አሳስበዋል።

ሩሲያ በአንድ ምሽት 367 ያህል ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) እንዲሁም ሚሳኤሎችን ተጠቅማ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል።

የሩሲያ እና ዪክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ በአንድ ሌሊት የተፈጸመ ከፍተኛው ጥቃት መሆኑ ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የድሮኖች እና ሚሳኤሎች ማስጠንቀቂያ ሳይረኖች በበርካታ የዩክሬን ግዛቶች ሰኞ ማለዳ ላይ በድጋሚ እየተሰሙ እንደሆነም ተነግሯል።

በሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ግዛት ህጻንን ጨምሮ ቢያንስ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የግዛቲቷ ከንቲባ ኢሆር ቴሬክሆቭ ተናግረዋል።

እሁድ አመሻሹ ላይ በኒውጀርሲ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ትራምፕ፤ ፑቲንን "ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ እንግባባለን። በአሁኑ ወቅት ግን ሮኬቶችን ወደ ከተሞች እያስወነጨፈ ሰዎችን እየገደለ ነው። በጭራሽ የምወደው ነገር አይደለም" ብለዋል።

አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማክበድ እያሰቡ እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ "በርግጠኝነት!" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በሞስኮ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ለማጥበቅ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ቢዝቱም ተግባራዊ ሲያደርጉት አይታይም።

ብዙም ሳይቆይ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ፑቲን "ፍጹም አብዷል" ሲሉ አስፍረዋል።

"የተወሰኑ ግዛቶችን ብቻ ሳይሆን መላዋን ዩክሬንን መጠቅለል እንደሚፈልግ ሁልጊዜም እናገር ነበር። ምናልባትም ይህ ትክክል ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። ነገር ግን ይህንን ካደረገ ሩሲያን ወደ ውድቀት ይመራታል" ብለዋል።

ትራምፕ የሩሲያውን አቻቸውን ብቻ ሳይሆን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ጠንከር ባሉ ቃላት ተችተዋቸዋል "እሱ የሚናገርበት መንገድ ለሃገሩ ምንም አይነት ፋይዳ እያደረገ አይደለም" ብለዋቸዋል።

"ከአፉ የሚወጡ ቃላቶች ሁሉ ችግር ፈጣሪ ናቸው። ደስ አይለኝም፤ እና ቢያቆመው ይሻላል" ሲሉ ትራምፕ ለዘለንስኪ ጽፈውላቸዋል።

የዩክሬን አውሮፓውያን አጋሮች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ቢያዘጋጁም አሜሪካ በበኩሏ የሰላም ድርድሮችን ለማሳለጥ እንደምትሞክር እና ይህ ፍሬያማ ካልሆነ ራሷን እንደምታወጣ ስትናገር ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት ትራምፕ እና ፑቲን አሜሪካ ጦርነቱን ለማስቆም ባቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለሁለት ሰዓታት ያህል በስልክ ተነጋግረው ነበር።