ዜሌንስኪ በዩክሬን ውስጥ 155 ቻይናውያን ለሩሲያ ጦር እየተዋጉ ነው አሉ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዩክሬን በርካታ የቻይና ዜጎች ከሩሲያ ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ መሆናቸውን ተናግረዋል

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዩክሬን ቢያንስ 155 የቻይና ዜጎች ከሩሲያ ጦር ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱ ይህ አስተያየት የተሰማው፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሁለት ቻይናውያን ወታደሮች በዩክሬን ከተያዙ በኋላ ነው ።

ይህ ቻይና ለሩሲያ የሰው ኃይል ትሰጣለች የሚለው የኪየቭ ይፋዊ ውንጀላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማ ነው።

ረቡዕ ዕለት ፕሬዝዳንቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዜሌንስኪ መንግሥታቸው በሰበሰበው መረጃ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ "እጅግ በርካታ" የቻይና ዜጎች አሉ በማለት በድጋሚ ተናግረዋል።

ቻይና ቀደም ሲል በርካታ ዜጎቿ ለሩሲያ እየተዋጉ ነው የሚለው ውንጀላ "በእውነታ ላይ ያልተመሠረተ" በማለት ውድቅ አድርጋ ነበር።

ቤጂንግ እስካሁን ድረስ ከዜሌንስኪ ለቀረበባት ውንጀላ ምላሽ አልሰጠችም።

ረቡዕ ዕለት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን "ከዩክሬን ጋር ያለውን መረጃ እያጣራን ነው" ያሉ ሲሆን፣ የቻይና ወታደሮች በግላቸው ተሳትፈው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሊን ጂያን እንዳሉት "የቻይና መንግሥት ሁል ጊዜ የቻይና ዜጎች የትጥቅ ግጭት ካለበት አካባቢ እንዲርቁ፣በየትኛውም ዓይነት የትጥቅ ግጭት ውስጥ እንዳይሳተፉ እና በተለይም በማንኛውም አካል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚናገር መሆኑን አፅንዖት መስጠት እፈልጋለሁ።"

በተጨማሪም ዩክሬን "ቻይና የዩክሬን ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ የምታደርገውን ገንቢ ሚና በትክክል እንድትመለከት" ጠይቀዋል።

ዜሌንስኪ "የቻይና ጉዳይ አሳሳቢ ነው" በማለት ውንጀላቸውን አጠናክረዋል።

ኢንተርፋክስ እንደዘገበው "ሙሉ ስማቸው ከእነ ፓስፖርት መረጃቸው የተመዘገበ 155 የቻይና ዜጎች አሉ። 155 የቻይና ዜጎች በዩክሬን ግዛት ከሩሲያ ጎን በመሆን እየተዋጉ ነው" ብሏል።

ዜሌንስኪ ሩሲያ የቻይና ዜጎችን በማኅበራዊ ሚዲያ እየመለመለች ነው ያሉ ሲሆን "የቤጂንግ ባለስልጣናት ስለዚህ ጉዳይ ያውቃሉ" ብለዋል።

እንደ ዜሌንስኪ ገለጻ ከሆነ፣ አዲስ ምልምሎች ወደ ዩክሬን ከመላካቸው በፊት በሞስኮ ስልጠና እንዲሁም የጉዞ ሰነዶች እና ክፍያ ይወስዳሉ።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩክሬን ጦር በአገሪቱ ምሥራቃዊ ዶኔትስክ ግዛት ስድስት የቻይና ወታደሮችን ጋር ውጊያ ገጥሞ፣ ሁለት መማረካቸው ተነግሯል።

ሩሲያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

የዩክሬን መሪ "ሩሲያ በዚህ በአውሮፓ ጦርነት ውስጥ ከሌሎች አገራት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሆን ቻይናን ማሳተፏ፣ ፑቲን ጦርነቱን ከማስቆም ይልቅ ሌላ ነገር ለማድረግ እንዳሰቡ ግልፅ ማሳያ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ ይህንን መረጃ "የሚረብሽ" ስትል ገልጻለች።

ዩክሬን ከዚህ ቀደም ቻይናን ገለልተኛ መሆኗን እንድትገልጽ ስትጠይቅ ነበር።

ዜለንስኪ ቀደም ሲል ቤጂንግ "ለሩሲያ የጦር መሣሪያ አካል የሆኑ ቁሳቁሶችን" ታቀርባለች በማለት አገሪቱ "ወጥነት ያለው" አቋም እንድትይዝ ጥሪ አቅርበው ነበር ።

አሜሪካ በበኩሏ ቻይና፣ሩሲያ ጥይቶችን፣የጦር ሜዳ ተሽከርካሪዎችን እና ሚሳኤሎችን እንድታመርት ትረዳለች ስትል ትከስሳለች።

ቤጂንግ እና ሞስኮ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ የቅርብ አጋሮች ቢሆኑም፣ ቻይና በግጭቱ ውስጥ ራሷን እንደ ገለልተኛ አካል ለማሳየት ትሞክራለች።

ለሩሲያ ሲዋጉ የተያዙት ቻይናውያን የተሰማው ዩክሬን የተጎዱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በሩሲያ ኩርስክ ግዛት መያዟን መግለጿ ተከትሎ ነው።

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በ2022 ነው ሁሉን አቀፍ ጦርነት ዩክሬን ላይ ያወጁት። ሩሲያ በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።