የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች በወሲባዊ ብዝበዛዎች የሚከሰሱባት ኮንጎ

ካማቴ ቢቢቼ

የአስራ ሁለት ዓመቱ ዲሚትሪ በምሥራቃዊቷ ኮንጎ፣ ጎማ በሚገኝ ቤት ውስጥ እናቱ ጋር ተደብቋል።

ሙቀቱ እፍን ቢያደርግም በቆርቆሮ ከተሠራችው ቤት ብዙም መውጣት አይፈልግም።

"የቆዳው ቀለም ቀይ በመሆኑ እና ፀጉሩ ለስላሳ ስለሆነ የሰፈር ልጆች እንዲያሾፉበት ስለማይፈልግ ነው" ትላለች እናቱ ካማቴ ቢቢቼ ለቢቢሲ።

"የዲሚትሪ አባት ሩሲያዊ ነው፤ ሆኖም ልጄ እውነተኛ ማንነቱን ሳይረዳ ሊያድግ ይችላል" ትላለች።

ታዳጊው ዲሚትሪ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማረጋጋት ተልዕኮ አባላት (ሞኑስኮ) በኮንጎ የፈጸሙት አሳዛኝ ክስተቶች ማስታወሻ ነው።

ተልዕኮው በጦርነት በምትናጠው ኮንጎ የተሰማራው በአውሮፓውያኑ 1999 ነው።

አባላቱ ከተሰማሩበት ጊዜ ጀምሮ በአዋቂ እና በታዳጊ ሴቶች ላይ መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ብዝበዛዎችን እና ጥቃቶችን ፈጽመዋል የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ካማቴ ከአልጋዋ ስር የተደበቀች አቧራማ ሳጥን ከማውጣቷ በፊት አመነታች።

የዲሚትሪ አባት ነው ያለችው ዩሪቭ ቀሪ ማስታወሻዎችን አወጣች፤ የነተበች የወታደር ኮፍያ እና አሮጌ ፎቶ።

ካማቴ እና ዩሪ የተገናኙት በአንድ ምሽት ነው።

ካማቴ በተረጋጋ ስብዕናው እንደተሳበች ትናገራለች። ሦስት ወራትን አብረው አሳለፉ።

"እሱ እንደሌሎቹ ወንዶች አልነበረም። ይወደኝ እና ይንከባከበኝ ነበር። በሕይወቴ ድንቅ የምላቸው ሦስት ወራት ናቸው" ትላለች ካማቴ።

ዩሪ ስለ ማንነቱም ሆነ ስለ ሥራው ምንም አልነገራትም።

ይህ ግን የዩሪ ብቻ ሳይሆን በኮንጎ የሰፈሩ በርካታ ሰላም አስከባሪዎች ከአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ጋር ሲገናኙ ደበቅ ባለ መልኩ ነው።

"የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ነበር" ትላለች ካማቴ።

"ነፍሰ ጡር መሆኔን አውቆ እንደሚንከባከኝ ቃል ገብቶ ነበር። ነገር ግን ያለ ምንም ቃል ደብዛው ጠፋ። ምንም አልመሰልነውም" በማለት ካማቴ ታስረዳለች።

ከዚህ ቀደም እሱን ታገኝበት የነበረው ስልክ ስለተቋረጠ ሩሲያዊ የልጇን አባት ለማግኘት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበራትም።

ምንም እንኳን ካማቴ ይህንን ግንኙነት የመሠረተችው በፈቃደኝነት ቢሆንም፤ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ 2005 ባጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ይህ እንደ ብዝበዛ ይቆጠራል።

ፖሊሲው በተበባሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች እና ተጋላጭ በሆነው የአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል ያለውን የኃይል አለመመጣጠን ከግንዛቤ ያስገባ ነው።

ይህ እንደ ካማቴ ያለው ግንኙነት በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ ቢመስልም የወሲብ ብዝበዛ ሊሆንም ይችላል።

ይህ የውሳኔ ሀሳብ ለተጎጂዎች ፍትህ ለማምጣት በሚል እነዚህ ጥቃት አድራሾች ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ወቅት በሕግ እንዲጠየቁ ያሳስባል።

የካማቴ ፍቅረኛ የት እንዳለ የተጠየቁት የመንግሥታቱ ድርጅት የኮንጎ የሰላም አሰከባሪ (ሞኑስኮ) ቃል አቀባይ ንዴዬ ሎ "በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩት ጥቂት የፖሊስ መኮንኖች እና ሠራተኞች ብቻ ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት ተናግረዋል።

ተልዕኮው በአውሮፓውያኑ 2012 ያገለገሉ የሩሲያ መኮንኖች መረጃዎችን "በሕጋዊ ጉዳዮች" ምክንያቶች መስጠት አንችልም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎቱን ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ጭምር ዩሪን ለማግኘት ቢሞክርም ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማረጋጋት ተልዕኮ  (ሞኑስኮ) አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማረጋጋት ተልዕኮ (ሞኑስኮ) አርማ

ከባባድ ክሶች

በማዕድን የበለጸገችው ምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ አማጽያን ከአገሪቱ መንግሥት ኃይሎች ጋር ለአስርት ዓመታት ተፋልመውባታል።

ግዛቲቷ በዘንድሮው ዓመት ጥር ወር በሩዋንዳ በሚደገፈው ኤም23 አማጺያን እጅ ወድቃለች።

ታጣቂዎቹ ከተማዋን ሲቆጣጠሩ ሰባት ሺህ ገደማ ሰዎች በጦርነቱ መሞታቸውን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት ከኮንጎ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ይህም በዓለማችን ከፍተኛው የአገር ውስጥ መፈናቀል ቀውሶች አንዱ ያደርገዋል።

በርካቶች በአስከፊ ድህነት ይማቅቃሉ።

እንደ ምግብ፣ ውሃ እና መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ፈተና በሆነባት ኮንጎ በተለይም ሴቶች እና ታዳጊዎች ለብዝበዛ የተጋለጡ ናቸው።

ቢቢሲ ማሪያ ማሲካን (ስሟ የተቀየረ) ባገኛት ወቅት የጦርነት ቀጣና ከሆነችው ሳኬ ከተማ ወደ ጎማ በመጣች ማግስት ነው።

ስፍራዋ የመንግሥት ወታደሮች እና አማጺያን ሲፋለሙባት የቆየች ናት።

በመጨረሻም አማጺያኑ አሸነፉ።

አሁንም ያለፈችበት የተኩስ እሩምታ ያባንናታል።

ማሲካ ለደኅንነት ስትል በጎማ እናቷ ጋር ያስቀመጠቻትን የስምንት ዓመት ልጇን ኪውንን ልታይ ነው የመጣችው።

ገና በ17 ዓመቷ ሚንጉኒ በተሰኘ የጦር ሰፈር የተመደበ ደቡብ አፍሪካዊ ሰላም አስከባሪ ጋር ግንኙነት ጀመረች።

"ለአካለ መጠን ያልደረስኩ ልጅ እንደሆንኩ ያውቅ ነበር" ስትል ታስረዳለች።

"በጦር ሰፈሩ አቅራቢያ ቤት ተከራይቶ ከሥራ ሲወጣ ይመጣ ነበር" ብላለች ማሲካ።

ሆኖም ልጇ ኩዊን ከተወለደች በኋላ ሰላም አስከባሪው ደብዛውን አጠፋ።

ልጇን ብቻዋን ለማሳደግ የተገደደችው ማሲካ ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ በወሲብ ንግድ ውስጥ ገብታለች።

በተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች እና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ስላለው ግንኙነት ከቢበሲ ጥያቄ የቀረበለት የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ኃይል ክሱን በጥብቅ እንደሚያየው ገልጿል።

"በተልዕኮ ስፍራዎቹ ያሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ተዓማኒ የሆኑ የወሲብ ብዝበዛዎችን፣ ጥቃቶችን እንዲሁም የዲሲፒሊን ጥሰቶችን ያያሉ" የመከላከያ ኃይሉ ቃል አቀባጥ ሲፒዌ ድላሚኒ ያስረዳሉ።

ባርኔጣ የያዘች ሴት

ብዝበዛዎችን አንታገስም

ኮንጎሊዝ ፋሚሊ ፎር ጆይ በተባለ የተተው እና ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት መጠለያ (ሴፍ ሐውስ) ከሰላም አስከባሪዎች የተወለዱ ቢያንስ አምስት ልጆች አሉ።

እነዚህ ህጻናት በእናቶቻቸውም የተተው ናቸው።

"ከአጋሮችን ጋር ሆነን በተመድ የኮንጎ ሰላም አስካበሪዎች (ሞኑስኮ) ሠራተኞች ወሲባዊ ብዝበዛ ለደረሰባቸው 200 ለሚሆኑ ሴቶች እና ታዳጊዎች ድጋፍ እንሰጣለን" ይላሉ የማዕከሉ ዳይሬክተር ኔሊ ክየያ።

"በርካቶቹ ከማኅበረሰባቸው በሚደርስባቸው ከፍተኛ መገለል የተነሳ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ወደ ወሲብ ንግድ ይገባሉ። ይህ መገለል ልጆቻቸውንም እንዲተዉ ያደርጋቸዋል" ይላሉ።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሴቶች መብቶች ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሶፌፓዲ ብሔራዊ አስተባባሪ ሳንድሪን ሉሳማባ እንደሚናገሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ወሲባዊ ብዝበዛ ፈጻሚዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ቀጥተኛ ሥልጣን ስለሌው አጥፊዎች ነጻ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ይላሉ።

በርካታ አባል ሀገራት ወታደሮቻቸውን ለመክሰሰስ እንደማይተባበሩ ያስረዳሉ።

ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግሥታት የወጣ ሪፖርት ከሰላም አስከባሪዎች እና ልዩ የፖለቲካ ተልዕኮዎች ጋር በተገናኘ የወሲባዊ ጥቃቶች እና ብዝበዛዎች መበራከታቸውን ያሳያል።

ከሁለት ዓመታት በፊት 100 ክሶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ይህም ከአውሮፓውያኑ 2022 ከነበረው 79 ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ነው።

በእነዚህ ዓመታት የተመዘገቡ ክሶች 143 የጥቃት ሰለባዎችን ያካተቱ ሲሆን፣ 115 አዋቂዎች እና 28ቱ ህጻናት መሆናቸውን ይኸው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያሳያል።

በተለይም እነዚህ ክሶች 90 በመቶ የሚሆኑት ከተመድ ሰላም አስከባሪዎች (ሞኑስኮ) ጋር መገናኘታቸው በተልዕኮው ውስጥ ስላለው ተጠያቂነት ስጋቶችን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

"የወሲባዊ ብዝበዛ እና ጥቃቶች ክሶች ሲደርሱን መረጃዎች ተገምግመው ተጨባጭ እርምጃ ይወሰዳል" ይላሉ የሞኑስኮ ቃል አቀባይ ንዴዬ ሎ።

"ክሶቹ የተረጋገጡበት ሠራተኛ በቀጣይ ስምሪቶች እንዳይሰማራ ወይም ሥራ ከመቀጠር እንዲታገድ የሚያደርግ ሥርዓት ዘርግተናል" ይላሉ።

ተልዕኮው ተጎጂዎችን እና ልጆቻቸውን በተጎጂዎች እርዳታ ትረስት ፈንድ በኩል ሥልጠና እና ትምህርት በመስጠት እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።