ዩክሬን ላደረሰችው የድሮን ጥቃት ፑቲን የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ትራምፕ አስጠነቀቁ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዩክሬን በሩስያ የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ ላደረሰችው ጥቃት ፑቲን የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ መናገራቸውን የአሜሪካው ፕሬዚዳንትንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።

ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ቆይታ የነበራቸው ዶናልድ ትራምፕ "ፑቲን በቅርቡ የሩስያ አየር ኃይል ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ መውሰድ አለብኝ ሲል አስረግጦ ነግሮኛል" ብለዋል።

የሩስያ ባለስልጣናት የትራምፕ አስተያየት እውነትነት ላይ አስተያየት ለመስጠት ቢቆጠቡም ቀደም ብሎ ሞስኮ ዩክሬን ላደረሰችው ጥቃት ወታደራዊ አጸፋ አንዱ አማራጭ መሆኑን ገልጻ ነበር።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር ካደረጉት ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀ የስልክ ንግግር በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰራጩት መልዕክት በሩስያ እና ዩክሬን መካከል ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰላም የሚመራ አይደለም ብለዋል።

የሩስያ መንግሥት የዜና አግልግሎት እንደዘገበው ከሆነ "ዩክሬን ድርድሩን ለማወክ እየሞከረች ነው" ሲሉ ፑቲን ለትራምፕ ተናግረዋል።

ጨምረው የኪዬቭ መንግስት ወደ አሸባሪ ድርጅትነት እየተለወጠ ነው ብለዋል።

ሁለት ፕሬዝደንቶች አሜሪካ እና ሩስያ በሚተባበሩበት ጉዳይ ላይ መነጋገራቸውም ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ዩክሬን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስርጋ ባስገባቻቸው ድሮኖች የሩስያ የጦር አውሮፕላኖች ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ፑቲን እና ትራምፕ ሲነጋገሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በዚህ የስልክ ውይይት አሜሪካ ስለጥቃቱ ቀድሞ እንዳልተነገራት ትራምፕ ለፑቲን መናገራቸውን የሩስያ ፕሬዝዳንት አማካሪ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምት ፑቲን ወደሰላም የሚመጡበትን የሁለት ሳምንት ቀነ ገደብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስቀምጠው ነበር። ይህ ካልሆነ ግን አሜሪካ በተለየ መንገድ ምላሽ እንደምትሰጥ ሲዝቱ ተስምተዋል።

ትራምፕ ይህንን ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ሩስያ የተጠናከረ የአየር እርምጃ እየወሰደች የነበረ ሲሆን ፑቲን በእሳት እየተጫወቱ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ከፑቲን ጋር ከተወያዩ በኋላ 'ትሩዝ ሶሻል' በተባለው ማኅበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፑቲን ወደ ሰላም እንዲመጡ ብለው ስላስቀመጡት ቀነ ገደብ ያሉት ነገር የለም።

ትናንት ረቡዕ የዩክሬን ምክትል ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒሰትሩን የያዘ የልዑክ ቡድን የአሜሪካ ሴናተሮችን ለማግኘት ወደ ዋሽንግተን አቅንቷል።

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የጉዞው ዓላማ የመከላከያ ድጋፍ ለማግኘት እና በጦርነት አውድማ ያለው ሁኔታ ለመግለጽ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩስያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ ማቆም የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ማድረጓን ገልጸዋል። ይህ ጥያቄ የዩክሬን እና አሜሪካን ጨምሮ የአጋሮቿ እንደሆነ ይገለጻል።

የሩስያ ተደራራዳሪዎች ደግሞ በተወሰኑ አካባቢዎች ለቀናት የሚቆይ የተኩስ ማቆም የሚል ሀሳብ እንዳቀረቡ ከመግለጽ ውጪ ተጨማሪ መረጃዎችን አልሰጡም።

በሌላ ዜና ፕሬዝዳንት ፑቲን ከቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

ቫቲካን ባወጣው መግለጫ በዩክሬን ሰላም ለማምጣት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አሳውቋል።