በሁለት የእርስ በርስ ጦርነቶች መካከል ራሳቸውን ያገኙት እናቶች እና ልጆች

የፎቶው ባለመብት, Hassan Lali / BBC
በሱዳን የሚካሄደው አውዳሚ ጦርነት በዋና ከተማዋ ካርቱም ሲደርስ ሳራ ዊሊያምስና ልጆቿ ከየአቅጣጫው ከሚሰማው የተኩስ እሩምታ ማምለጫ ቀዳዳ ማግኘት አልቻሉም ነበር።
ጥይቶች ቤታቸውን በሳሱት፣ ሕንጻዎች በእሳት ጋዩ፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች እዚህም እዚያም ፈንድተው ከጥቅም ውጭ ሆኑ።
"ትርምስ ነበር። መሬት ላይ በደረታችን እየተሳብን ነበር" ትላለች የአንድ ዓመት ልጇን ወደ ደረቷ እያስጠጋች።
የ33 ዓመቷ ሳራ የአምስት ልጆች እናት ስትሆን ደቡብ ሱዳናዊት ናት።
አዲሷ አገር ከሱዳን ነጻነቷን ካገኘች ከሁለት ዓመታት በኋላ እአአ በ2013 ወደ እርስ በርስ ጦርነት ስትገባ ሳራ ጨርቄን ማቄን ሳትል ተሰደደች።
የነጻነቱ ፈንጠዝያ አጭር ነበር። በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ጦርነት ተጀመረ።
400 ሺህ የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እና 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉበት የእርስ በርስ ጦርነት የተወለደው በስልጣን ሽኩቻው መካከል ነው።
ሳራ እግሮቿን ወደ ሱዳን ስታነሳ፣ በወቅቱ ካርቱም ሰላም ነበረች። መካከለኛ ገቢ ላለው ቤተሰብ የቤት ሠራተኛ ሆና መሥራት ዕጣ ፈንታዋ ሆነ።
እአአ በ2023 በሱዳንም ጦርነት ተቀሰቀሰ። በሱዳን ጦር መሪ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ታማኝ ኃይሎች እና በወቅቱ ምክትላቸው በነበሩት መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በድጋሚ አፈናቀላት።
"ግጭቱ የተጀመረው እርስ በርሳቸው ነው። በኋላ ግን እኛ የጦርነቱ አካል ባንሆንም ደቡብ ሱዳናውያንንም መግደል ጀመሩ" ትላለች ሳራ።
በሱዳን በተነሳው ግጭት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል። የካርቱምን አብዛኛውን ክፍልም ወደ ፍርስራሽነት ቀይሮታል።
ቤቷ ጥቃት ሲደርስባት ጥቂት ንብረቶቿን ጠቅልላ ጥላት ወደ መጣችው ወደ ደቡብ ሱዳን ተመለሰች።
አሁንም በደቡብ ሱዳን ግጭት ተቀስቅሷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2018 በኪር እና በማቻር መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የመፍረስ ስጋት እንደተጋረጠበት አስጠንቅቋል።
የሳራ ጉዞ ሬንክ አድርሷታል። በአንድ ወቅት ፀጥታ የሰፈነባት አቧራማዋ የድንበር ከተማ ከሁለቱ ሱዳኖች የመጡ ስደተኞችን የሚጎርፉባት መተላለፊያ ሆናለች።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Lali / BBC
ለአምስት ወራት ያህል በሬንክ የቆየችው ሳራ በላይኛው ናይል ግዛት ወደሚገኘው የትውልድ መንደሯ ናስር መመለስ ትፈልጋለች።
ወደ ናስር መጓዝ ግን አደገኛ ነው። ናስር የሶባት ወንዝ ዳር ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ ላይ የምትገኝ የወደብ ከተማ ናት። አሁን ወደ ጦርነት አውድማ በመቀየሯ ጉዞዋን አስቸጋሪ አድርጎታል።
"ከፊታችን ግጭት አለ" ስትል የአራት ዓመት ልጇን ይዛ የአንድ ዓመት ወንድ ልጇን አዝላ ለቢቢሲ ትናገራለች።
ድምጿ የተረጋጋ ነው። አይኖቿ ግን የጦርነትን፣ ኪሳራን እና እርግጠኛ አለመሆንን በመሸከማቸው ተዳክመዋል።
የመንግሥት ወታደሮች እና ነጩ ጦር (በእርስ በእርሱ ጦርነት ወቅት ከማቻር ጋር የወገነው የሚሊሺያ ቡድን) በናስር በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
ጥቃት፣ የሽምቅ ውጊያ እና ድብደባ በመኖሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ታውቋል።
ሳራ በከተማዋ ስለሚገኙት ቤተሰቦቿ ምንም የሰማችው የለም።
"ግጭቱ ሲጀመር ወደ የት እንደሚሸሹ አላውቅም… ወይም በሕይወት ስለመኖራቸው እንኳ አላውቅም" ትላለች ዝግ ባለ ድምጽ።
በደቡብ ሱዳን ያለው ጦርነት እንደ ሳራ ያሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሬንክ መተላለፊያ ማዕከል ውስጥ እንዲቆዩ አስገድዷል።
ካምፑ ተጨናንቋል። ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎችን ያስተናግዳል። ይህም ከታሰበው ቁጥር በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ነው።
ስደተኞች በእርዳታ ኤጀንሲዎች በኩል ምግብ እንዲገዙ ትንሽ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።
ገንዘቡ ለሁለት ሳምንታት ብቻ የሚበቃ ሲሆን ከዚያ በኋላ ራሳቸው መቻል ይጠበቅባቸዋል።
ሳራ እና ሌሎች ስደተኞች ለምግብ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ዛፎችን በመቁረጥ የማገዶ እንጨት ለመሸጥ እንደተገደዱ ተናግራለች።
"ዱቄት ለመግዛት የማገዶ እንጨት እየሰበሰብኩ እሸጥ ነበር። አሁን ግን ጫካው ውስጥ የቀረ ነገር የለም። ሴቶች የሚሰበስቡበት እና የሚሸጡት እንጨት የለም" ብላለች።
ይህም ጦርነት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ውድመት የሚያሳይ ነው።
በጣብያው ውስጥ ባሉ የቆርቆሮ መጠለያዎች በአንድ ክፍል እስከ 15 ሰዎች ይታጨቃል።
ሌሎች ደግሞ ከእንጨት፣ከጨርቃ ጨርቅ እና ከተቀደደ ከረጢት ቤቶችን ይገነባሉ። ከአቅም በላይ የሆነው የስደተኞች ቁጥር በሽታ፣ ረሃብ እና ተስፋ መቁረጥን እያስከተለ ነው።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ባልደረባ የሆኑት ቪጃያ ሶሪ እንዳሉት ከሆነ የረድኤት ተቋማት ስደተኞችን የተሻለ መተጋገዝ ወዳለባቸው የደቡብ ሱዳን ሰላማዊ አካባቢዎች ለማዛወር እየሞከሩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Lali / BBC
ወደ ማላካል የሚሄዱትን የብረት ጀልባዎች ለመሳፈር በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በጠራራ ፀሀይ ይጠባበቃሉ።
በአባይ ወንዝ ላይ የሚደረገው ጉዞ ሁለት ቀን ተኩል ይፈጃል።ተሳፋሪዎቹ በሻንጣቸው ወይም በጀልባው ወለል ላይ ይቀመጣሉ።
ከእነዚህም መካከል በሱዳን ግጭት ወቅት ከዋድ ማዳኒ የተፈናቀለችው ሜሪ ዴንግ ትገኝበታለች።
"ድንበሩን ስንሻገር ይህ ልጅ ገና አንድ ቀኑ ነበር። በአጠቃላይ 16 ነን ምንም ገንዘብ አልነበረንም፣ ፈጣሪ ግን ነበረን" ትላለች።
ዶክ ከነቤተሰቦቿ ከሬንክ የሚወጡበትን በርካታ ቲኬቶች ይዛ ነበር።
የሕክምና አገልግሎቶች ከአቅማቸው በላይ ሆኗል። በቆርቆሮ የተሠራው የጆዳ ድንበር ክሊኒክ በአካባቢው ብቸኛው አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ጣቢያ ነው።
"ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ከ600 በላይ ሕፃናት እዚህ ተወልደዋል። አሁን ግን መሥራት የምንችለው በቀን ውስጥ ብቻ ነው።
ለለሊት ፈረቃ ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ የለም" ሲሉ አንድ የጤና ባለሙያ ተናግረዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር በሬንክ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ታውጆ ነበር። ዋና ከተማዋን ጁባ ጨምሮ በደቡብ ሱዳን አብዛኛው ክፍል ተዛምቶ ከ450 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።
በደቡብ ሱዳን የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ኦፊሰር ታጠቅ ወንድሙ ማሜቻ እየጨመረ ያለውን አደጋ በተመለከተ አስጠንቅቀዋል።
"ምንም እንኳን የኮሌራ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ቢውልም ገና ሙሉ ለሙሉ ስጋቱ አልተቀለበሰም። አሁን ወባ እየጨመረ ነው። የዝናብ ወቅት በመድረሱ ቁጥሩ ይጨምራል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዓለም አቀፍ ዕርዳታን በመቀነሱ ምክንያት እየደረሰ ያለው ተፅዕኖ እጅግ አስከፊ መሆኑን ታጠቅ ጨምረው ገልጸዋል።
"አምስት አጋሮቻችን አገልግሎቱን አቁመዋል ወይም ድጋፋቸውን በ 50 በመቶ ቀንሰዋል።"
እንደ ሬንክ ሪፈራል ያሉ ሆስፒታሎች ግማሽ ሠራተኞቻቸውን አጥተዋል።
"ተቋሙ በቀን ከ350 እስከ 400 የሚደርሱ ሰዎችን ያክማል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Lali / BBC
በሬንክ ያለው የስደተኞች ቀውስ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሁለት ግጭቶች መካከል መያዛቸውን እና ለሁለት ዓመታት በሱዳን የዘለቀውን ግጭት ሸሽተው ለሚሰደዱ ሰዎች ደቡብ ሱዳን አስተማማኝ መሸሸጊያ ቦታ አለመሆኗን አሳይቷል።
ማቻር የታጠቁ ቡድኖችን ይደግፋሉ በሚል የኪር አጋሮች ከሰዋቸው የቁም እስረኛ ከሆኑበት ከመጋቢት ወር ጀምሮ በደቡብ ሱዳን ውጥረቱ ተባብሷል።
የማቻር ፓርቲ ግን ክሱን አስተባብሏል።
የ2018 የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የተቋቋመው የክትትል አካል ሊቀመንበር ጆርጅ ኦዊኖ በበኩላቸው የአሁኖቹ ግጭቶች "የስምምነቱን መሰረት አደጋ ላይ ይጥላሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዋናው ችግር የፖለቲካ መሪዎች ተቀናቃኝ ወታደሮችን ወደ አንድ የተዋሃደ ብሄራዊ ጦር ማዋሃድ ባለመቻላቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በፖለቲካ እና በወታደራዊ ሃይል መካከል ያለው ግንኙነት አሁንም አልተለወጠም" ብለዋል ኦዊኖ።
"መሪዎች አለመስማማት ሲጀምሩ በፍጥነት ወደ ትጥቅ ግጭት ይቀየራል። ይህን ደግሞ ስምምነቱ መከላከል ነበረበት።"
እአአ በ 2013 የእርስ በርስ ጦርነት የተቀሰቀሰው ኪር ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ማቻርን በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከስሰው ከስልጣን ሲያነሷቸው ነበር።
ማቻር ደግሞ ኪርን "አምባገነን" ናቸው በማለት ክስ አቅርበዋል።
እአአ በ2018 የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ማቻር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በመሾማቸው አስከፊው የእርስ በርስ ጦርነት አበቃ።
"የበለጠ ውይይት ሊኖር ቢገባም ቀንሷል" ሲሉ ኦዊኖ ተናግዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ሂደቱ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመለስ ያደረገው ጥረት እስካሁን ያልተሳካ ሲሆን ኡጋንዳ በበኩሏ ኪርን ለመደገፍ ወታደሮቿን ወደ ደቡብ ሱዳን አሰማርታለች።
የማቻር ፓርቲ የኡጋንዳን ውሳኔ የደቡብ ሱዳንን ሉዓላዊነት እና የ2018ቱን የሰላም ስምምነትን የሚጎዳ ነው ብሏል።
ኡጋንዳም ሆነች ኪር በሁለቱ አገራት መካከል በቆየው የጸጥታ ስምምነት መሰረት የተከናወነ ነው በማለት ተከላክለዋል።
የኡጋንዳ ጦር መሰማራት የኪር የስልጣን ምን ያህል ደካማ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን የእርስ በርስ ጦርነት እንደገና ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረም ይገኛል።
በሱዳን በኩል ደግሞ የእርስ በርስ ጦርነቱ እንደቀጠለ ሲሆን ጄኔራል ዳጋሎ ትይዩ መንግሥት መመስረቱን አስታውቀዋል።
እርምጃው የተሰማው ጦራቸው ከከባድ ውጊያ በኋላ ካርቱምን ላይ ከተሸነፈ በኋላ ነው። ከተማዋ አሁን የፈራረሱ ህንጻዎች መቃብር ሆናለች።
ሳራ ወደ ካርቱም የመመለስ ሃሳብ እንደሌላት ተናግራለች። "ሁኔታው መጥፎ ቢሆንም" በትውልድ አገሯ ሕይወቷን እንደገና መግፋት የተሻለ እንደሆነ ወስናለች።